top of page

አቶ ጃዋር መሐመድ ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸው ተገለፀ

ፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በትናንት ውሎው በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና 14 ተጠርጣሪዎች የቅድመ ምርመራ መዝገብ ባለፈው ቀጠሮ የተሰጡ ትዕዛዞችን አፈፃፀምና የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ነበር ትናንት፣ ሐሙስ (ነሐሴ 14 2012) ቀጠሮ የያዘው።

በትናንትናው ዕለትም ባለፈው ቀጠሮ ተሰጥተው ከነበሩ ትዕዛዞች አንደኛው ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲደረግላቸው የሚል ነበር።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም ከኢትዮጵያ ጤና ኢንስቲትዩት የተላከ የኮቪድ-19 ምርመራ ውጤት ማስረጃን ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። በማስረጃው መሠረት አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ ሃምዛ አዳነ (ቦረና) እና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸው በችሎቱ ላይ ተነግሯል።

በሌላ በኩል፣ በሌላ ቀጠሮ ትዕዛዝ ተሰጥቶበት የነበረው የአቶ ጃዋር መሐመድ የሕክምና ጉዳይ ነበር። ፍርድ ቤቱ አቶ ጃዋር መሐመድ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

አቶ ጃዋር መሐመድ በትናንቱ ችሎት ሕክምና እንዳላገኙ እና አሁንም እየታመሙ እንደሆነ "ምግብ ስበላ ያስመልሰኛል፤ ያስቀምጠኛል" በማለት የጤንነታቸውን ሁናቴ አስረድተዋል።


አቶ ጃዋር ለህይወታቸው ካላቸው ስጋት የተነሳ በማያውቁት ሃኪም መታከም እንደማይፈልጉ ጨምረው ተናግረዋል።

በተለይ "ሃጫሉ ሞቷል፤ ጃዋር ነው የቀረው እየተባለ ነበር። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም ህይወቴ ላይ ስጋት ስላለ ነው ጥብቅ ጥበቃ እያደረገልኝ ያለው፤ እኔም የመንግሥት የሕክምና ተቋማትን ንቄ ሳይሆን ለሕይወቴ ካለኝ ስጋት አንጻር ነው በግል ሀኪሜ መታከም የፈለግሁት" ሲሉ አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ጀዋር መሐመድ ሰኞ ዕለት መርማሪ ፖሊስ እና አቃቤ ሕግ እርሳቸው ጋር በመገኘት የግል ሐኪማቸውን ጠርተው መታከም እንደሚችሉ ነግረዋቸው የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ግን የሐኪማቸው ስልክ ስላልነበራቸው በነጋታው መጥተው እንዲያክሟቸው ቢጠሯቸውም እንዲያክሟቸው እንዳልተፈቀደ እና እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አቃቤ ሕግ "በወቅቱ አስቸኳይ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ከነበር ሐኪማቸውን ጠርተው እንዲታከሙ ነግረናቸው ነበር። ይሁን እንጂ ስልካቸው የለኝም በማለት ሊታከሙ አልቻሉም። ከዚያ ውጪ ግን ባለው ደንብ መሰረት ነው መታከም ያለባቸው" በማለት ለችሎቱ አስረድቷል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም አቶ ጃዋር መሐመድ በፌደራል ፖሊስ ሪፈራል ሆስፒታል ሁኔታዎችን ማመቻቸቱንና እዚያ የሚታከሙ ከሆነም "ለሕይወታቸው ዋስትና" እንደሚሰጥ ተናግሯል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 21 በመጥቀስ፣ አቶ ጃዋር መሐመድ በግል ሐኪማቸው የመታከም መብት እንዳላቸው ይህም እንዲፈፀም ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል በተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው በኩል እንደ ቅሬታ ሲነሳ የነበረው የካሜራ ጉዳይ ነው።

ይህም ጠበቆች ደንበኞቻቸውን የሚያናግሩበት ስፍራ ላይ ምስልና ድምጽ የሚቀርጽ ካሜራ በመገጠሙ ምስጢራቸው በተጠበቀ መልኩ ደንበኞቻቸውን ማናገር እንዳልቻሉ ነሐሴ 11 2012 በነበራው የችሎት ውሎ ላይ ተናግረው ነበር።

ፍርድ ቤቱም ጠበቆች ደንበኞቻቸውን ምስጢራቸው በተጠበቀ መልኩ ማግኘት እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ጠበቆች ትናንት ለችሎቱ እንዳስረዱት፣ ደንበኞቻቸውን ለማነጋገር ሰኞ፣ ረብዑ እና አርብ ቀጠሮ እንደተያዘላቸው ገልፀው ረብዑ እለትም ወደ ስፍራው ባመሩበት ወቅት ካሜራው እንደተገጠመ መሆኑን መመልከታቸውን ገልፀው ስልክ ቁጥራቸውን ትተው ሲስተካከል እንዲጠሯቸው በመንገር መመለሳቸውን ገልፀዋል።

በእለቱም (ረብዑ 13/2012) ወደ አስር ሰዓት አካባቢ ተደውሎላቸው መጠራታቸውን፣ ይሁን እንጂ በመምሸቱ የተነሳ ደንበኞቻቸውን ሳያነጋግሩ መመለሳቸውን ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ባይሳ ለችሎቱ ተናግረዋል።

"ዛሬ እንዳነጋግራቸው ነው ተነጋግረን የተመለስነው፤ ዛሬ ጠዋት ስንሄድ ደግሞ ያለ ቀናችሁ ነው የመጣችሁት ገብታችሁ ማናገር አትችሉም ተብለን ተመልሰናል እና ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እያከበረ አይደለም" በማለት እንዲስተካከልላቸው በመጠየቅ ለችሎቱ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

ፖሊስ በበኩሉ የተገጠመው ካሜራ ቤተ መጻህፍትን ለመጠበቅ እንደሆነ በመናገር፣ ጠበቆች ከደንበኞቻቸው ጋር እንዲገናኙ ሌላ ስፍራ ማመቻቸታቸውንና መገናኘታቸውን ለዚህም ደግሞ ጠበቆች ወደ ቅጽር ግቢው ገብተው ደንበኞቻቸውን ሲያናግሩ የፈረሙበትን መዝገብ ማቅረብ እንደሚችሉ ለችሎቱ ተናግሯል።

ይሁን እንጂ ጠበቆች "ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ገብተን ደንበኞቻችንን አናግረን ስንወጣ ነው የምንፈርመው አሁን ገና ደንበኞቻችንን ሳናገኝ እንድንፈርም ይደረጋል፤ ገና ወደ ውስጥ ስንገባ፥ ሳናገኛቸው እየተመለስን ነው" ብለዋል።

ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን አድምጦ፣ ጠበቆች ደንበኞቻቸውን ምስጢሩ በተጠበቀበት ስፍራ ማግኘት አለባቸው። ይህም መፈፀም አለበት፤ ይህ ካልተፈፀመ ግን ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድ በመግለጽ ውሳኔ ሰጥቷል።

በስተመጨረሻም ችሎቱ የተጠርጣሪዎች እንዲሁም የአቃቤ ሕግ አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት እንዲሁም ደግሞ የአቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለነሐሴ 18 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የጋዜጠኛ መለሰ አቤቱታ እና የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ

ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የቅድመ ምርመራ መዝገብ ሥራ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በሙሉ የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ይሁን እንጂ የኦኤምኤን ጋዜጠኛው አቶ መለሰ ዲሪብሳን ጨምሮ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ስር ለሚገኙ ለአራት ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራው አለመካሄዱን ጠበቃው አቶ ዋቤ ሐጂ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጋዜጠኛ መለሰ፤ "ከእኛ ጋር ታስረው የነበሩ ሰዎች በኮሮና ተይዘዋል። ፍርድ ቤቱም ከዚህ ቀደም ምርመራ እንዲደረግልን አዞ ነበር። ይሁን እንጂ እስካሁን ምርመራ አልተደረገልንም። ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እያከበረ አይደለም" ሲሉ ለችሎቱ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አቶ መለሰ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ቤተሰቦቻቸውን በስልክ እያገኙ መሆኑን እና እርሳቸው ግን ይህን መከልከላቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱም ለተጠርጣሪዎች አቤቱታ ምላሽ ለመስጥት እና ተጨማሪ የአቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን ለመስማት ለሰኞ ነሐሴ 18 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።


Comments


Post: Blog2_Post

GH ETHIO NEWS.COM

Your Go-To Source

We are all told, “live your life to the fullest”; I am here to do just that. GH ETHIO NEWS.COM serves as a vessel to project my passions, and clue in my loyal readers as to what inspires me in this crazy world. So, sit back, relax, and read on.

Post: Welcome

Subscribe Form

Thanks for submitting!

0936323517

©2020 by GL NEWS AMHARIC.COM. Proudly created with Wix.com

bottom of page