በስድስት ወንዶች የተደፈረችው ታዳጊ ሰቆቃ
- GH ETHIO NEWS
- Aug 20, 2020
- 6 min read
ዝናቡ ሳይበግራቸው በጠዋት ነበር የህክምና ባለሙያዎች የጎዳና ተዳዳሪ ሴት ህጻናት መከላከያ ተሃድሶና መቋቋሚያ ግቢ የደረሱት።
በድርጅቱ ከ20 በላይ በተለያየ ዕድሜ የሚገኙ ህጻናት እና ሴቶች ይገኛሉ። (ስለተወሰኑት ህጻናት በቅርቡ እንመለስባቸዋለን።)
የህክምና ባለሙያዎቹ የወቅቱን ትኩሳት ኮቪድ-19 ለመመርመር ነው የተገኙት።
መጀመሪያ ህክምና የተደረገላት 10 ዓመት የሚሆናት ልጅ ናት። ቀጥሎ ደግሞ የዛሬዋ ባለታሪክ።
ምርመራዋን አጠናቅቃ ከደቂቃዎች በኋላ መጣች። 17 ዓመቷ እንደሆነ ነው የተነገረን።
የአፍና በአፍንጫ ጭንብል እድርጋ ነው የመጣችው። ቁመናዋን ስንመለከት ግን 17 ዓመትም የሞላት አትመስልም።
ማህሌት አበበ (ለዚህ ታሪክ ሲባል ስሟ የተቀየረ) እንደምትባል እና ዕድሜዋ በትክልልም 17 እንደሆነ ገለጸችልን።
ውልደቷም ዕድገቷም ምዕራብ ጎጃም ነው።
ትምህርቷንም ዕድሜዋ እስከሚፈቅድላት ድረስ ገፍታለች። (ሁሉንም መረጃዎች የጠየቅናት ቢሆንም እንዳንዶቹን ማንነቷ በቀላሉ እንዳይለይ ለማድረግ አስቀርተናል።)
ትምህርቷን ለመቀጠል ነበር ወደ ባህር ዳር ያቀናችው። ይህ ጉዞዋ ከቤተሰብ አባላት 'ይሁን' ተብሎ የተፈቀደ ነበር።
በተለያየ ምክንያት ትምህርት የመቀጠል ህልሟ ሊሳካ አልቻለም።
ሌላ ውሳኔ። ሌላ እርምጃ። ሌላ አማራጭ። ፊቷን ወደ ሥራ አዞረች።
"የተገኘውን እሠራ ነበር። ፑል ማጫወትም ጀምሬ ነበር። ቀጥሎ ግሮሰሪ ላይ ማስተናገድ ጀመርኩኝ" ስትል ያለ እድሜዋ ብዙ ሥራዎችን መሥራቷን ትናገራለች።
ሥራውን ለማግኘት ብዙም አልከበዳትም። በሚያውቋት እና አሠሪዎቿን በሚያውቁ ሰዎች ነው ሥራዎቹን ያገኘችው።
መጨረሻ ላይ የሠራችው በአንድ አነስተኛ ግሮሰሪ ነበር።
ረቡዕ ሰኔ 10/2012። የተለመደው ቀን ነበር። ስለ ዕለቱ ስታወራ ትንሽ ዝም ከማለት ውጭ ከጀመረች በኋላ ያለማቋረጥ ታሪኳን ታጫውተን ጀመር።
በኮሮና ምክንያት ሥራ አቁመን ስለነበር ዝም ብዬ ቤት ነበርኩ።
10 ሰዓት ሲሆን እንደተለመደው አየር ለመቀበል 'ዎክ' ለማድረግ ወጣሁ።
ጉዞ ደግሞ ወደ ጣና ሆነ። ወጣሁኝ። ሰፈር ጓደኛዬ ነበር። ትንሽ ዎክ አድርገን ነፋስ ተቀብለን ሳይመሽ ወደ ቤት እንመጣለን ተባብለን ወጣን።
አብሯት ያለው የፍቅር ጓደኛዬ አይደለም። ሰፈር ውስጥ የማውቀው ጓደኛዬ ነው።
10፡30 አካባቢ ይሆናል። ሰፈር ውስጥ በዓይን ብቻ የማውቀውን ልጅ ሠላም አልኩት።
ከልጁ ጋር ምንም አይነት ቅርርብም የለንም። ከእሱ በተጨማሪ ሁለት ጓደኞቹም አብረውት ነበሩ።
ሁለቱ ጓደኛዬን ሳብ አደረጉትና አስቀሩት። እሱ [ጓደኛዬ] የዚህ ሃገር [ባህር ዳር] ልጅ ስለሆነ የሚያውቁት ነው የመሰለኝ። ስሙን ጠርተው ወደ ኋላ ሳቡት። እሱን ለካ አባረውታል እኔን ይዘውኝ ሄዱ።
በዓይን የምታውቀው ልጅ እያወራ አብሯት ሲሄድ 'ጓደኛዬ አይመጣም ወይ?' እያልኩ ዞር ብዬ አይ ነበር።
[በዓይን ብቻ የማውቀው ልጅ] ቁጭ ብሎ በሠላም ሲያዋራኝ ቆየ። 'የምን ሃገር ልጅ ነሽ? ምንድነው የምትማሪው? ሥራ እንዴት ነው? እያለ ሲጠይቀኝ ቆየ።
እሱ በሥራ ልብስ ነበር። የጋራዥ ልብስ ለብሶ ነበር።
በኋላ 'ልሄድ ነው' አልኩት። 'ልሄድ ነው' ስለው 'አይ የትም አትሄጂም' አለኝ። 'ለምን?' ስለው 'ከእኔ ጋር የሆነ ቦታ ትሄጃለሽ' አለ።"
እኔ 'የትም አልሄድም' ስለው አስፈራቶ ጩቤ ምናመን አውጥቶ የሆነ ቦታ ወሰደኝ። [ባህር ዳር] ቀበሌ 3 ማለት ነው። ጩቤ ይዞ እያስፈራራኝ ነበር። ሁለቱ ጓደኞቹ መጡ። ጓደኛዬ ግን የለም። ጩቤ ጎኔ ላይ ይዞ ነው የወሰደኝ። መጮህም አልቻልኩም ብትነፍሺ ወየውልሽ እያለ ያስፈራራኝ ነበር።
አንድ ቤት ይዞኝ ሄደ። ትልቅ ግቢ ነው የቆርቆሮ አጥር አለው። ቤቱ ፍርስርስ ያለ የጭቃ ቤት ነበር። ሰው አይኖርበትም። እዚያ ወሰደኝ።
ስንገባ ደግሞ 3 ልጆች አገኘን። ከእነሱ ጋር ሠላም ተባባለ። እኔን 'ሂጂ ተቀመጪ' ሲለኝ 'አልቀመጥም' ስለው 'አንቺ ተቀመጪ ቀበጥሽ' ብለው አስፈራሩኝ። በጥፊ ሁሉ መቱኝ።
ሰፈር ውስጥ የማውቀው ልጅ ሌሎቹን ከግቢው ውስጥ አስወጣቸው። ግቢው በጣም ትልቅ ነው። እኔ እያለቀስኩ ነበር።
'ነይ' አለኝ 'ምንድነው?' ስለው። 'ሁሉም ጓደኞቼ ያሰቡት እየመጡ ካንቺ ጋር ግንኙነት ሊያደርጉ ነው። እኔ ደግሞ ያ እንዲሆን አልፈልግም ምክንያቱም በሰፈር ስለማውቅሽ እንደዚህ እንዲሆን አልፈልግምና እነሱ እንዳይመጡ መጀመሪያ ከእኔ ጋር ግንኙነት ማድረግ አለብሽ' አለኝ።
በአይን እንጂ አላውቀውም። ስሙንም ያወቅኩት ሲጠሩት ነው።
'ከእኔ ጋር ግንኙነት አድርገሽ ላስወጣሽ' አለኝ። 'አልፈልግም' አልኩት። 'እነሱም ማድረግ ፈልገዋል' አለኝ። 'እረ በእናትህ ብዬ' ብዙ ለመንኩት።
'ምን አይነት ነሽ? በሁሉም መደፈር ፈልገሽ ነው?' ብሎ ሰደበኝ። 'እኔ እንደዛ ፈልጌ አይደለም። ግን አልፈልግም' ብዬ ያላቀረብኩት ምክንያት የለም። ከዚያ 'አላውቅልሽም' ብሎ በጥፊ መታኝ።
ቤቱ ጋደም ያለ ነው። መሬቱ አፈር ነው። በጭቃ ነው የተሰራው። ፍርስርስ ያለ ነው በጣም። ምንም የተነጠፈ ነገር የለም። 'ተኚ' አለኝ። 'ተኚ ልብስሽን አውልቂ' ሲለኝ 'እምቢ' አልኩት።
የቅድሙን ጩቤ አወጣና 'በዚህ ነው የምዘለዝልሽ' አለኝ። 'እምቢ' ስለው በጣም ብዙ ታገለኝ። ቱታ ነበር የለበስኩት። ሰፊ ቱታ ነበር። እሱን በ 'እንደዚህ ነው ራቁትሽን የምልክሽ' ብሎ በጩቤ ቀዳደደው።
እየወጋጋ ብጥርቅ ብጥርቅ እያደረገ ብዙ ቀዳደደው። አለቀስኩ። እንደምንም እየታገለኝ እየመታኝ በእግሩ እየረጋገጠ [ወሲብ ፈጽሞ] ከጨረሰ በኋላ 'ነይ ላስወጣሽ' ብሎ እጄን ያዘኝ።
'በሠላም ቢሆን ኖሮ እንደዚህም አትጎጂም። ልብስሽም አይቀደድም' አለኝ። 'በሠላም ከእኔ ጋር ብታደርጊ ኖሮ እንደዚህ አታለቅሺም' አለኝ።
ፊቴ አብጦ ነበር። 'እስኪ ተጎዳሽ?' እያለ ሲያይልኝ 'አትንካኝ' እያለኩ እያለቀስኩ እጄን ጎትቶ ወሰደኝ። መቶኝ ስለነበር ነው [ፊቴ] ያበጠው። ሆዴንም ረግጦኛል። እምቢ እያልኩት ነበር [የደፈረኝ።] ታግዬዋለሁ። ተኝቼም ብዙ ይመታኝ ነበር።
ከዚያ እጄን ጎትቶ ወደ ግቢው አስወጣኝ። ግቢው መሃል ላይ 'ቁሚ እዚህ' አለኝ። 'ለምን?' ስለው 'ላስወጣሽ አይደል? እነሱ [ግቢ ውስጥ የነበሩ ሌሎች ጓደኞቹ] መኖራቸውን ልይ' አለኝ። ፈርቼ ከኋላው ከኋላው ተከተልኩት። ለካ ጓደኞቹ ውጭ ነበሩ። አውቆ ነበር እንደዚያ ያለኝ። በሩን ከፍቶ 'ቻው' ብሎ ስቆብኝ አለ አይደል አላግጦ 'ቻው' ብሎ ወጥቶ ሄደ።
ከዚያ አምስቱ ተከታትለው ገቡ። ከዚያ 'እረ በማርያም ብዬ ኡኡ' ብዬ ጮኽኩኝ።
[ከአምስቱ] 3ኛው ልጅ 'አንቺ ቀበጥሽ' ብሎ እንትን ነገር ቆረጠ። ግቢው በጣም ሰፊ ነው፤ ዛፍ ምናምን አለው። ሽመል ነገር ቆርጦ 'አልቀበጥሽም?' ብሎ መታኝ።
አንደኛው እጄን ይዞኝ '[የመጀመሪያውን ልጅ ስም ጠቅሶ] ስለኔ አላወራሽም' አለኝ? 'እረ ምንም አላወራኝም' አልኩት። 'ነይ ግቢ' ብሎ ሁሉም ካደረጉ [ወሲብ አብረውኝ ከፈጸሙ] በኋላ ወጥተው ሄዱ መጨረሻ ላይ።
በወቅቱ [ሲደፍሩኝ] በጣም ያመኝ ነበር። መሃል ላይ ራሴን ስቼ ነበር። የሚያደርጉትን ግን አውቃለሁ። ከሦስተኛው በኋላ መታገል አቃተኝ። ራሴን መታኝ። አንዱ ደረቴን ሲመታኝ ጸጥ አልኩኝ። ውሃ ሁላ ደፍተውብኛል። ውሃ ደፍተውብኝ ሲቆነጥጡኝ ሁላ አልሰማም። አያቸዋለሁ ግን አልሰማም ነበር። ሲቆነጥጡኝ አላመመኝም። በጥፊ ሁላ ይመቱኛል። ግን ምንም አያመኝም ነበር። ምን እንደሚያደርጉ አያቸው ነበር። ሰውነቴ ዛለ። ሰውነቴን መቆጣጠር አልችልም ነበር። ውሃ ከደፉብኝ በኋላ ነቃሁ። በጣም ታምሜ ነበር በሰዓቱ በጣም።
ስድስት መሆናቸውን አውቃለሁ ምክንያቱም ራሴን ስቼ ሰውነቴን ባልቆጣጠርም ልጆቹ ምን እንደሚያደርጉ አይ ነበር።
ስልኬ ዝግ ነበር። እነሱ ነበሩ ስልኬን የያዙት። ቀምተውኝ ስልኩን ዘግተውታል። መጨረሻ ላይ አበሩት እና 'በይ ሂጂ። የሆነ ነገር ብተነፍሺ አታመልጪንም' ብለው አውጥተው ወረወሩኝ። ጸጉሬንም አራገፉልኝ። እንደአጋጣሚ ስልኬ ሲበራ ጓደኛዬ ደወለ። እኔም አነሳሁትና 'ናልኝ' አልኩት።
እየሮጠ መጣ። አንድ የማውቀውን ልጅ ከሴት ጓደኛው ጋር አገኘሁት። አንደኛው ልጅ [ከደፈሩኝ አንዱ] እየተከተለኝ ነበር እና ያዝልኝ አልኩት። ሆኖም በጨለማው ገብቶ አመለጠ።
የማውቀው ልጅ እያለቀስኩ ስለነበር የተመታሁ ብቻ ነው የመሰለው። 'ወደ ህክምና ልውሰድሽ' ሲለኝ 'አልፈልግም ወደ ጣቢያ ውሰደኝ' አልኩት። ጣቢያ ወሰደኝ። ህክምና ተደረገልኝ ቃሌንም ተቀበሉኝ። ጣቢያ አደርኩ። ከዚያ ወደዚህ [ድርጅት] መጣሁ በነጋታው።
እንቅልፍ አልተኛሁም። ሲያመኝ፣ ሳቃስት ነበር። 'ሽንት ቤት ልሂድ ብዬ አምልጬ ራሴን ላጥፋ' ብዬ የዛን ቀን ምሽት ላይ በጣም ብዙ ሳስብ ነበር። ራሴን ማጥፋት አለብኝ ብዬ ብዙ አስቤያለሁ።
ከዚያ በኋላ ሽንቴን መሽናት አልችልም ነበር። ለስድስት ቀን ሽንቴን መሽናት አልቻልኩም ነበር። ማሕጸኔ ላይ በጣም ያመኝ ነበር። እዚህ ከመጣሁ በኋላ ህክምና ተደረገልኝ። ቱቦ ተተክሎልኝ በዚያ ነበር የምሸናው። ለሦስት ቀን ተበሎ ነበር ቱቦው የገባልኝ። ሆኖም በሁለተኛው ቀን በጣም አመመኝ። በጣም ሲያምኝና ደምም ሲፈሰኝ ቱቦው በሁለተኛው ቀን ተነቀለልኝ። ስሽና የህመም ስሜት ነበር። አሁን ደህና ነኝ።
ከዚህ ከመጣሁ በኋላ በጣም አመመኝ። ሽንቴ እምቢ አለ። ጨነቀኝ። በጣም ያመኝ ነበር ማህጸኔ ላይ። ሽንቴን መሽናት ሲያቅተኝ ስታመም ሐኪም ቤት ሄድኩኝ። ከዚህ ከመጣሁ በኋላ ብዙ ህመም ነበርኝ። ከዚያ ተሻለኝ።
ወደዚህ ድርጅት አንዲት የፖሊስ ባልደረባ ናት የላከችኝ። 'ሁሉም ነገር እስኪጠናቀቅ በማዕከሉ ሁኚ' ብላ።
ፖሊሶቹ [የወሊድ] መቆጣጠሪያ ወዲያው ሰጡኝ ሌላውን ምርመራ ሁሉንም ነገር አድርጌያለሁ። የኤችአይቪ ምርመራ ከሦስት ወር በኋላ አሉኝ።
አምስቱ ተይዘዋል። አንዱ አምልጧል። እኔም ፍርድ ቤት ሄጄ ቃሌን ሰጥቻለሁ። አምስቱም ቀርበው ነበር።
ወደ ማዕከሉ ሰኔ 11 ነው የመጣሁት። ወደ ማዕከሉ ከመጣሁ አንድ ወር ሆነኝ። ብዙ እንክብካቤ ከልጆቹ የተለየ ህክምና ተደርጎልኛል። ሽንቴን መሽናት ሲያቅተኝ የግል ሃኪም ዘንድ ወሰዱኝ። መድሃኒቴን ሰዓት እየጠበቁ ይሰጡኝ ነበር። በጣም ተንከባክውኛል።
አሁን ወንድ ልጅ ራሱ ሳይ በጣም ነው የሚያስጠላኝ። ማርያምን። አዕምሮዬ በጣም ነው የተነካው። አሁን ሰውነቴ ጋር ምንም ችግር የለብኝም። እጄ በጣም በልዞ ነበር። ፊቴ አብጦ ነበር። በድርጅቱ እገዛ በጣም ተሽሎኛል። አሁን ደህና ነኝ። በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለሁት።
ወደፊት ቤተሰብ ጋር ሄጄ ትምህርቴን መማር እፈልጋለሁ ቢስተካከልኝ።
ሴቶችን ማለት የምፈልገው እንጠንቀቅ ለእንደዚህ አይነት ነገር እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ። ወንዶችን ደግሞ ቢያንስ ከሴት ነው የተፈጠርነው እናት እህት ሊኖረን ይችላል እንደዚህ ዓይነት ጉዳት ባይደርስ እላለሁ። ለህግ አካላት ደግሞ ተገቢውን ፍርድ እንዲሰጡ እላለሁ።
ቤተሰቦቼ አልሰሙም። እንዲሰሙም አልፈልግም። እነሱ እንዲጨነቁ ስለማልፈልግ እንዲሰሙ አልፈግልም።
አንድ ዘመዴን በፊት የደፋሪዎቹ ቤተሰቦች እንደራደር እያሉ ያስቸግሯት ነበር።
ቢቢሲ፡ በምንድነው እንደራደር የሚሉት?
ማህሌት፡ በገንዘብ። በፊት ላይ ማለት ነው ገንዘብ እንስጥሽ እና ክሱን አቁሚ ይሉ ነበር።
ቢቢሲ፡ እና ለምን አልደራደርም አልሽ?
ማህሌት፡ በገንዘብ መደራደር አልፈልግም፤ ምንክያቱም እኔ ይሄን ነገር በገንዘብ ተደራድሬ ባልፍ ነገ ደግሞ እህቶቼ አሉ እንደዚህ የሚደረፈሩ። ያ እንዲሆን አልፈልግም በእኔ የደረሰው ጉዳት በሌሎች እንዲደርስ አልፈልግም።
የጎዳና ተዳዳሪ ሴት ህጻናት መከላከያ ተሃድሶና መቋቋሚያ ድርጅት በተለያየ ምክንያት ጥቃት የሚደርስባቸውን ህጻናት ይረዳል። ከ2000 ዓ.ም ጀምሮም የህጻናቱን መሠረታዊ ፍላጎት ከማሟሏት ባለፈ የስነልቦና ድጋፍ ያደርጋል።
ህገ ወጥ የህጻናት ዝውውር፣ ያለዕድሜ ጋብቻ እና ወሲባዊ ትንኮሳ የደረሰባቸው ሴቶች በብዛት ወደ ድርጅቱ ይሄዳሉ። ድርጅቱ ከሴቶቹ ባለፈ ቤተቦቻቸውን በማማከር የተሻለ ህይወት እንዲመሩ ያግዛል። ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ለሚታይም ከለላ በመስጠት ውሳኔ እንዲያገኙ ያግዛል።
ጥቃት የደረሰባቸው ህጻናት እና ሴቶች ወደ ድርጅቱ የሚመጡት በፖሊሶች አማካይነት ነው።
ማህሌትንም ወደ ድርጅቱ ያመጧት የባህር ዳር ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አባላት ናቸው።
ዋና ሳጅን ቢራራ ሞላ የባህር ዳር ከተማ የስድስተኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ ናቸው።
"በ17 ዓመቷ ማህሌት ላይ በቀን 10/10/2012 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡30 እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ድረስ ነው ወንጀሉ የተፈጸመባት" ሲሉ ጉዳዩን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ወንጀሉ ከተፈጸመባት በኋላ ጉዳዩ ወደ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ግለሰቧ ወደ ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ሄዳ በቂ ህክምና ተደርጎላት ወደ ጣቢያ መመለሷን ገልፀው፣ ምርመራው በነጋታው መቀጠሉን አስታውቀዋል።
ሰኔ 11 ጀምሮ በተደረገ የምርመራ ሥራ የተጠርጣሪዎች ስም ማወቅ በመቻሉ "ሁሉም የፖሊስ ሰራዊት በመረባረብ አምስቱ ሲያዙ፣ አንዱ ሳይያዝ ቀርቷል" ብለዋል።
"በአምስቱ ላይ ምርመራው ቀጥሎ የህክምና ማስረጃውንም አምጥቶ ዕድሜያቸውንም በማስመርመር፣ ሁሉም ከ17 ዓመት በላይ የሆኑና ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በከፊል አምነዋል፣ በከፊል የካዱ ቢሆንም የህግ ማስረጃዎች ግን በወቅቱ የተፈጸመውን ነገር በሚገባ አስረድተው ስለነበር ተከሳሾችን በቁጥጥር ስር አውለን መዝገባችንን አጠናቀን ለባህር ዳር ከተማ ፍትህ ቢሮ ልከን መዝገቡ ተከፍቷል" ብለዋል።
"የሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ አንገብጋቢ ስለሆነ" በዚህ ውስጥ የባህር ዳር ፍትህ ቢሮ ፍርድ ቤትን ጨምሮ በቂ እገዛ እንዳደረጉላቸው አስታውቀዋል።
መዝገቡ ተከፍቶ ከተመሠከረ በኋላ ለመከላከያ ሲባል ተከሳሾች ወደ ማረሚያ ቤት እንዲሄዱ ፖሊስ ጠይቋል። በተጠየቅነው መሠረትም ፍርድ ቤት ጉዳዩ አሳማኝ ነው ብሎ ስላመነ ተጠርጣሪዎች ወደ ባህር ዳር ከተማ ማረሚያ ቤት እንዲገቡ ተደርጓል።
ስድስተኛውን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ለማዋል እና "ሁሉም ተቋማት በመተባበር እና በመረባረብ በመዝገቡ ላይ በመሳተፍ ውሳኔ እየጠበቅን ነው" ብለዋል።
Kommentare