ዶናልድ ትራምፕ ፡ "ውሸታምና ሥነ ሥርዓት የሌለው ሰው ነው" የዶናልድ ትራምፕ እህት
- GH ETHIO NEWS
- Aug 24, 2020
- 2 min read
የዶናልድ ትራምፕ ታላቅ እህት ወንድማቸው 'ቀጣፊና ሥነ ሥርዓት ያልፈጠረበት መደዴ ሰው' እንደሆነ ተናገሩ፡፡
ሜሪያን ትራምፕ ቤሪ ስለ ታናሽ ወንድማቸው ዶናልድ ትራምፕ ይህን ያሉት በድብቅ በተቀዳ የድምጽ መረጃ ነው፡፡
እንዲህ ሲሉ በድብቅ የቀዷቸው ደግሞ የታላቅ ወንድማቸው ሴት ልጅ የሆነችውና በቅርቡ አነጋጋሪ መጽሐፍ ያሳተመችው ሜሪ ትራምፕ ናት ተብሏል፡፡
ሜሪ ትራምፕ ባለፈው ወር ዶናልድ ትራምፕን ክፉኛ የሚያብጠለጥል መጽሐፍ ጽፋ ከፍተኛ መነጋገርያ ሆኗል፡፡ ዋይት ሐውስ መጽሐፉ እንዳይሰራጭ ያደረገው ሙከራም አልተሳካለትም፡፡
በዚህ መጽሐፍ በምንጭነት የተጠቀሱት የትራምፕ እህት ሜሪያን ትራምፕ ቤሪ ደግሞ ቀድሞ የፌዴራል ዳኛ የነበሩ ሴት ናቸው፡፡
የትራምፕ እህት ስለ ወንድማቸው ቀጣፊነት በተናገሩበት በዚህ የተቀዳ ድምጽ፣ ‹‹…በዚያ ላይ ስድ ትዊቶቹ፣ በዚያ ላይ የውሸታምነቱ ብዛት፣ የፈጣሪ ያለህ…! ወንድሜኮ የለየለት አስመሳይ እና ጨካኝ ሰው ነው…›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በቅርቡ መጽሐፍ ያሳተሙት የዶናልድ ትራምፕ ታላቅ ወንድም ልጅ ሜሪ ትራምፕ የዶናልድ ትራምፕን እህት ለምን በድምጽ መቅዳት እንዳስፈለጋት ስትናገር ‹ወደፊት ከሚመጣ ክስ ራሴን ለመከላከል ነው› ብላለች፡፡

ትራምፕ በዋይት ሀውስ በኩል ስለ ጉዳዩ በሰጡት ምላሽ ‹‹እና ምን ይጠበስ?›› የሚል ይዘት ያለው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
እህትየው ስለ ትራምፕ ተናገሩት ስለተባለው የተቀዳ ድምጽ መጀመርያ የዘገበው ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ሲሆን አሶሲየትድ ፕሬስ ቅጂውን ቀድሞ ማግኘቱን ተከትሎ ነው ዋሺንግተን ፖስት ዘገባውን ያወጣው፡፡
ስለ አጎቷ ዶናልድ ትራምፕና ስለ ቤተሰቧ መጽሐፍ የጻፈችው ሜሪ ትራምፕ ድሮ አጎቷ ትራምፕ ስለሱ መጽሐፍ እንድጽፍለትና በሱ ስም እንዲታተም ይለምነኝ ነበር ብላለች፡፡
ምንም እንኳ ቤተሰብ ቢሆኑም፣ ምንም እንኳ የወንድሙ ልጅ ብሆንም በጾታ ፍላጎት ያየኝ ነበርም ስትል አጋልጣለች፡፡
"ዶናልድ ትራምፕ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ያለፉት ከፍለው ነው"
በዚህ የተቀዳ ድምፅ እህት ቤሪ ትራምፕ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በስደተኞች ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ ሲተቹ ይሰማሉ፡፡ በድንበር አካባቢ ሕጻናትን ማጎርያ ውስጥ ማስቀመጥ አግባብ እንዳልሆነም ያስረዳሉ፡፡
‹‹ወንድሜ ይህን የሚያደርገው ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? (አክራሪ ብሔርተኛ የሆኑ) ደጋፊዎቹን ለማስደሰት ነው››
የሜሪ ትራምፕ የቤተሰባቸውን ትዝታዎችን የዘገበው አዲሱ መጽሐፍ "Too Much and Never Enough: How My Family Created the World's Most Dangerous Man" ይሰኛል፡፡
መጽሐፉን የጻፉት የትራምፕ የእህት ልጅ ሜሪ ትራምፕ ናቸው፡፡
ይህ መጽሐፍ ከያዛቸው አስደንጋጭ መረጃዎች መሀል ዶናልድ ትራምፕ እንዴት ዩኒቨርስቲ እንደገቡ የሚያትተው ክፍል ይገኝበታል፡፡
ሜሪ በዚህ ማስታወሻቸው አጎቷ ዶናልድ ትራምፕ የቅርብ ጓደኛቸውን ዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና (SAT) እንዲፈተንላቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደከፈሉት አስታውሰዋል፡፡
በገንዘብ ሀይል ፈተናውን ካለፉ በኋላ በፎርድሀም ኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ ከተመደቡ በኋላ ወደ ፔኒስልቬኒያ ዩኒቨርስቲ ማስቀየራቸው ተጠቅሷል፡፡
የዶናልድ ትራምፕ እህትም ወንድማቸው ዩኒቨርስቲ ፈተና ያለፈው በገንዘብ ኃይል ሰው እንዲፈተንለት አድርጎ እንደሆነ መስክረዋል፡፡
ይህ ድሮ የትራምፕ ጓደኛ የነበረውንና የዩኒቨርስቲ ፈተና እንዲፈትንለት ወንድማቸው ዶናልድ ትራምፕ ረብጣ ዶላር የከፈሉት ሰው በስም ጭምር እንደሚያስታውሱት ያወሳሉ፡፡
‹‹ወንድሜ ራሱ ተፈትኖ አይደለም ያለፈው፡፡ ሰው ከፍሎ አስፈትኖ ነው ፔኒሲልቬኒያ ዩኒቨርስቲ መግባት የቻለው›› ብለዋል ሜሪ፡፡
የትራምፕ እህት ከዚህ በፊት ወንድማቸው ዶናልድ ትራምፕ እንዴት ታመው በነበረ ጊዜ እንደተንከበከቧቸው ገልጸው በልጅነታቸውም ሁለቱ በጣም ይቀራረቡ እንደበረና ጠያቂ ወንድም እንደሆኑ መስክረውላቸው ያውቃሉ፡፡
ይህንን አነጋጋሪ መጽሐፍ የጻፈችው ሜሪ፣ ዶናልድ ትራምፕ አጎቷ ናቸው፡፡
ሜሪ አሁን 55 ዓመቷ ሲሆን የዶናልድ ትራምፕ ታላቅ ወንድም የነበሩትና በ1981 ዓ.ም የሞቱት የፍሬድ ትራምፕ ትንሹ ሴት ልጅ ናቸው፡፡ የሜሪ አባትና የዶናልድ ትራምፕ ወንድም ፍሬድ ትራምፕ ትንሹ የሞቱት ገና በ42 ዓመታቸው ነበር፡፡
ከፍተኛ የመጠጥ ሱሰኛ በመሆናቸው ከዚሁ ጋር ተያይዞ በልብ ህመም ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በ2016 የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ያወቅኩ ለታ 'ለዚህች አገር አነባሁ' ብላለች ሜሪ፡፡ እንደዚያን ቀን ደንግጣ እንደማታውቅም ተናግራለች፡፡
Comentarios