የኮቪድ-19 ገደብ ተላልፈው ሲጨፍሩ የነበሩ 13 ወጣቶች ሞቱ
- GH ETHIO NEWS
- Aug 24, 2020
- 1 min read
በላቲን አሜሪካዋ አገር ፔሩ ነው ይህ አሳዛኝ ክስተት የተፈጸመው፡፡
በአንድ መሸታ ቤት በር ዘግተው የልደት ድግስ አሰናድተው፣ "አስረሽ ምቺው" ላይ የነበሩ ወጣቶች ፖሊስ ይደርስባቸዋል፡፡
በፖሊስ መከበባቸውን ሲያውቁ በመሸታ ቤቱ አንዲት ቀጭን በር በኩል ለማምለጥ ሩጫ ይጀመራል፡፡
በዚህ ጊዜ ነው መረጋገጥና መተፋፈግ ተፈጥሮ ለሳቅ ለጨዋታ እንዲሁም ለደስታ የመጡ 13 ሰዎች ሕይወት እንዲህ እንደዋዛ ያለፈው፡፡
ፖሊስ ድንገተኛ ወረራ ያደረገው ጥቆማ ደርሶት ነው፡፡
በኮቪድ-19 ምክንያት ሰዎች ተሰብስበው እንዳይጨፍሩ የፔሩ መንግሥት እገዳ ከጣለ ሰነባብቷል፡፡
በሊማ፤ ሎስ ኦሊቮስ በሚባለው ሰፈር ቶማስ ሬስቶባር ናይት ክለብ ነው ይህ አሳዛኝ አደጋ የደረሰው፡፡

የአይን እማኞች እንደሚሉት ፖሊስ አስለቃስ ጭስ ተጠቅሟል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ እኔ አልተኮስኩም ሲል ተከራክሯል፡፡
ፕሬዝዳንት ማርቲን ቪዝካራ እንደተናገሩት በመሸታ ቤቱ ውስጥ አሸሼ ገዳሜ ሲሉ ከነበሩና ምርመራ ከተደረገላቸው 23 ወጣቶች ውስጥ 15ቱ ተህዋሲው ተገኝቶባቸዋል፡፡
ፔሩ ከደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ ኮቪድ ክፉኛ ካጠቃቸው ተርታ ትመደባለች፡፡ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ተህዋሲው የያዛቸው ሲሆን 27ሺ ሰዎች ሞተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ነው ካለፈው መጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ሰአት እላፊ የታወጀው፡፡
የፔሩ የአገር ውስጥ ሚኒስትር እንዳሉት የቅዳሜውን የልደት ድግስ 120 ሰዎች ታድመውበት ነበር፡፡
በጭፈራ ላይ የነበሩት ወጣቶች ፖሊስ መምጣቱን ሲያውቁ በደረጃው ላይ ቀድመው ለማምለጥ ሙከራ ላይ በነበሩበት ጊዜ ነው መጨፈላለቁ ተፈጥሮ አደጋው ሊደርስ የቻለው፡፡
ከ13ቱ ሟቾች ውስጥ ሁለቱ ሴቶች ናቸው፡፡
የመሸታ ቤቱ ባለቤት የሆኑት ባልና ሚስት ለጊዜው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
Comments