ባራክ ኦባማ "ትራምፕ አሜሪካን ላይ ቀልዶባታል" አሉ
- GH ETHIO NEWS
- Aug 20, 2020
- 2 min read
ሦስተኛ ቀኑን በያዘው ታላቁ የዲሞክራት ፓርቲ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ተተኪያቸውን ዶናልድ ትራምፕን አብጠልጥለዋል፡፡
‹ሰውየው አሜሪካ ላይ ቀልዷል፤ አገሪቷም የመራትም የመዝናኛ የቴሌቪዥን ትእይንት (Reality show) እንደሚመራ አድርጎ ነው፡፡› ብለዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት በተለያዩ የቴሌቪዥን የመዝናኛ ትእይንታዊ መርሐግብሮች ላይ በመሳተፍ፣ እንዲሁም በመዳኘት ይታወቃሉ፡፡
‹ያሳዝናል፣ ተተኪዬ ከመዝናኛ ትእይንት መሪነት ከፍ ሊል አልቻለም፣ ምክንያቱም ስለማይችል፡፡› ብለዋል ኦባማ፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ወዲያው በሰጡት ምላሽ ‹‹አንተ ያቦካኸውን ለማጽዳት እኮ ነው ሕዝብ የመረጠኝ›› የሚል መንፈስ ያለው ነገር ተናግረዋል፡፡
በሦስተኛ ቀን ምሽቱ የዲሞክራቶች ታላቅ ጉባኤ ካማላ ሐሪስ የምክትል ፕሬዝዳንትነት እጩነቷን በይፋ ተቀብላለች፡፡

ዛሬ ሐሙስ የጉባኤው መዝጊያ ሲሆን የዲሞክራቶች እጩና የትራምፕ ተገዳዳሪ ጆ ባይደን የማሳረጊያ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ባይደንና ሐሪስ በመጪው ኅዳር የሚፋለሙት ከዶናልድ ትራምፕና ምክትላቸው ማይክ ፔንስ ጋር ይሆናል፡፡
በዛሬው ጉባኤ አምርረው የተናገሩት ባራክ ኦባማ ንግግራቸውን ያቀረቡት ከፊላደልፊያ ሆነው ነው፡፡
‹‹ዶናልድ ትራምፕ በነጩ ቤተመንግሥት ውስጥ ስለራሱና ስለጓደኞቹ ሲጨነቅ ነው አራት ዓመታትን ያጠፋው፤ ለአሜሪካ ሕዝብ ምን ፈየደለት?››ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
‹‹…በዚህ ሰውዬ ፕሬዝዳንት መሆን የተነሳ በዓለም ስማችን ጎድፏል፣ አንጀታችን ቆስሏል፣ የዲሞክራሲ ተቋሞቻችን አደጋ ላይ ወድቀዋል›› ሲሉ ትራምፕን አውግዘዋል፡፡
‹‹…አሜሪካዊያን ሆይ! ይህ ሰው ሲቀልድባችሁ ዝም ብላችሁ አትመልከቱት፣ ዲሞክራሲያችሁን ሲቀማችሁ፣ አገራችሁን ሲነጥቃችሁ ቆማችሁ አትዩት፤ ድምጻችሁን ተጠቀሙበት፤ ባይደንን ምረጡ›› ብለዋል፡፡
ባራክ ኦባማ ገና ከነጩ ቤተ መንግሥት ሳይወጡ ከአራት ዓመት በፊት ስለ ትራምፕ መመረጥ ተጠይቀው ‹‹አሜሪካዊያን ይህንን ሰው ከመረጡማ ለኔ ውርደት ነው፤ እኔ እንደ ስድብ ነው የምመለከተው›› ብለው ነበር፡፡
ያን ጊዜ ትራምፕ የሪፐብሊካን እጩና ‹‹ዘ አፓረንቲስ›› የሚሰኝ የቴሌቪዥን አዝናኝ ትእይንት አቅራቢ ነበሩ፡፡
44ኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የፈሩት ደርሶ ትራምፕ ሰተት ብለው ነጩ ቤት መንግሥት ገቡ፡፡ የኦባማን ውርሶችም አንድ በአንድ ማውደም ያዙ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር ኦባማ ወደ ሚዲያ ወጥተው መናገር የጀመሩት፡፡
ሰኞ በተጀመረው ታላቁ የዲሞክራቶች ጉባኤ ሚሼል ኦባማ ባደረጉት ንግግር ‹‹ትራምፕ የጤና እርዳታ የሚሻ ሰው ነው፣ብቃት የሚባል ነገር አልፈጠረበትም›› ብለው ነበር፡፡
የሚሼል ኦባማ ንግግር አነጋጋሪ የሆነው በተለምዶ ቀዳማዊት እመቤቶች የሚያደርጓቸው ንግግሮች በተቻለ መጠን ከፖለቲካዊ መንፈሶች የጸዱ እንዲሆኑ ስለሚጠበቅ ነው፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ኦባማ ስለርሳቸው በተናገሩት ላይ ‹‹ምን የሚሉት ነገር አለ?›› ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡
‹‹እሱ ትቶልን የሄደው ኮተት ነው ለዚህ የዳረገን›› ብለዋል፡፡
‹‹ተመልከቱ እንዴት ቀሽም መሪ እንደነበረ፣ እንዴት ሥራ አይችል እንደነበረ፣ እንዴት ብቃት ያልፈጠረበት ከንቱ ሰው እንደነበረ›› ብለዋል ዶናልድ፣ ባራክ ኦባማን፡፡
‹‹…እኔ ፕሬዝዳንት የሆንኩት እኮ የሱን ኮተት ለማጽዳት ነው፡፡ የሱና የጆ ባይደንን ቆሻሻ›› ብለዋል፡፡
ይህን ንግግራቸውን ተከትሎ በትዊተር ሰሌዳቸው ‹‹እንኳን በሰላም መጣችሁልኝ ባራክና ያቺ ቀጣፊዋ ሂላሪ፣ በትግል ሜዳው ያገናኘን› የሚል ዛቻ የሚመስል ነገር ጽፈዋል፡፡
ሒላሪ ክሊንተን በዚህ የዲሞክራቶች ጉባኤ ላይ ከኒውዮርክ ቤታቸው ሆነው ባደረጉት ንግግር ‹‹ትራምፕ የተሻለ መሪ ቢሆን ደስ የለኝ ነበር፡፡ ግን እሱ በቃ ይኸው ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹ሰዎች ሲያገኙኝ እንዲህ አሳፋሪ መሪ ይሆናል ብለን አልጠበቅንም ነበር፣ ምነው ድምጽ በሰጠንሽ፣ ምነው አንቺን መርጠን ቢሆን፣ ምናለ ያኔ አውቀን ቢሆን ይሉኛል፡፡ …አሁን እንዲህ ባረኩ ኖሮ፣ እንዲያ ባረኩ ኖሮ ማለት አያስፈልግም፡፡ ባይደንን ድምጽ ስጡት›› ብለዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በቀጣይ የሪፐብሊካን ፓርቲ ዳግማዊ እጩ ተደርገው በይፋ በፓርቲያቸው ይሰየማሉ፤ ሥነ ሥርዓቱንም በዋይት ሐውስ አጸድ ላይ ይከወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
Коментарі