ታዳጊው ሱዳናዊ ስደተኛ አስከሬን በፈረንሳይ ባህር ዳርቻ ተገኘ
- GH ETHIO NEWS
- Aug 20, 2020
- 1 min read
የ16 አመት ሱዳናዊ ስደተኛ አስከሬን በፈረንሳይ ባህር ዳርቻ ተገኝቷል።
ታዳጊው ከፈረንሳይ ወደ እንግሊዝ በትንሽ ጀልባ ሊያቋርጥ ሲል ጠፍቶ የነበረ ሲሆን የስደተኞች መናኸሪያ በሆነው ካላይስ መገኘቱንም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
ሌላ ስደተኛ በዚሁ ዳርቻ መገኘቱንም ተከትሎ ነው ፍለጋው የተጀመረው።
ይኸው ግለሰብ መዋኘት የማይችለው ጓደኛው መጥፋቱን ተናግሯል።
ትንሿ ጀልባ በስደተኞች ታጭቃ የነበረ በመሆኑም ወደ ጎን አጋድላ የተወሰኑት ውሃው ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።

የፈረንሳይ ሚኒስትር ማርሊን ሺያፓ የታዳጊው አስከሬን በዛሬው ዕለት መገኘቱን የገለፁ ሲሆን ሰጥሞም በውሃው እየተገፋ ወደዳርቻው ተገፍቷል ብለዋል።
በታዳጊውም መሞት በርካቶች ኃዘናቸውን የገለፁ ሲሆን ቻሪቲ ኬር ፎር ካላይስ የተባለው ድርጅት ተወካይ ክሌር ሞስሌይ የታዳጊውን ሞት "በጣም አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ" ብለውታል።
"ምን ያህል ፈርቶ ይሆን? በጣም ያሳዝናል፤ ለቤተሰቦቹም መፅናናትን እንመኛለን" ብለዋል።
ድርጅታቸው የሚደግፋቸው ታዳጊዎቹ ስደተኞች በርካቶዎቹ በትምህርታቸው ጎበዝ፣ አንዳንዶቹ እግር ኳስ የሚወዱ፣ መፅሃፍ የሚያነቡና ያለፉበትን ሰቆቃና መከራ ረስተው ነገን በተስፋ የሚያዩ ናቸው ይላሉ።
"ማንም ቢሆን በእንዲህ አይነት መንገድ ብቻን በባህር መሞት አይገባውም" ብለዋል።
የእንግሊዙ ቀይ መስቀል ዋና ስራ አስፈፃሚ ማይክ አዳምሰን በበኩላቸው "ሰዎች አማራጭ አጥተው እንዲህ አደገኛ የሆኑ ጉዞዎችን ለማድረግና ጥበቃ ለመፈለግ ይህን ያህል መስዋዕትነት ሊከፍሉ መገደድ የለባቸውም" ሲሉ አስረድተዋል።
የእንግሊዝ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ እንዳሉት የታዳጊው ስደተኛ ሞቶ መገኘት "ህገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ምን ያህል ተጋላጭ ማህበረሰቦችን እንደሚበዘብዙ በሚያሳዝን መልኩ የሚያስታውስ ነው" ብለዋል።
የእንግሊዝ ባለስልጣናት ታዳጊው ወደ እንግሊዝ ለመድረስ እየተጓዘ ነው ከማለት ተቆጥበዋል።
በዚህ አመት 4 ሺህ 800 ስደተኞችን የያዙ 360 ትንንሽ ጀልባዎች ወደ እንግሊዝ ገብተዋል።
የሌበር ፓርቲ ፓርላማ አባል ቶማስ ስይሞንድስ በበኩላቸው በጀልባ ለሚያቋርጡ ስደተኞች የመንግሥታቸው ምላሽ "ኃዘኔታን ያጣና በቂ አይደለም" ሲሉ ተችተዋል።
በርካታ ስደተኞችም ህይወታቸውን እያጡም እንደሆነም ገልፀዋል።
እየተከሰተ ላለው ቀውስም ሰብዓአዊ መፍትሄ ለማምጣት ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር እንዲሰሩም ለሚኒስትሮች ጥሪ አቅርበዋል።
Comentários