ኬንያዊ ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ከእስር እንዲወጣ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።
- GH ETHIO NEWS
- Aug 20, 2020
- 2 min read
ከሰሞኑ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኬንያዊ ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ከእስር እንዲወጣ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል። ከዚህ ቀደም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ያሲን ጁማን ጨምሮ ሌሎች አስራ አንድ ሰዎች በዋስ እንዲወጡ ብይን ሰጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ፖሊስ ያሲን ጁማን በሌላ ወንጀል ጠርጥሬያለሁ በማለት በእስር አቆይቶታል። ከዚህ በፊት በነበሩ ሳምንታትም ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ ፖሊስ ሳይለቅ ያቆያቸው ተጠርጣሪዎች ነበሩ። ይህ ከሕግ አኳያ እንዴት ይታያል?
የሕግ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት ታምራት ኪዳነ ማሪያም ለዚህ ምላሽ አላቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት ፍርድ ቤት እንዲለቀቁ ትዕዛዝ የሰጠባቸውን ጉዳዮች ፖሊስ አለቅም የማለት ሥልጣን የለውም።
"አንዳንዴ ፍርድ ቤት ልቀቅ አትልቀቅ የሚል ውዝግብ ውስጥ ሳይገባ ፖሊስ ተጠርጣሪን በእስር ይዞ ለማቆየት ያቀረበለትን ጥያቄ [የጊዜ ቀጠሮ] አልቀበልም የሚልበት ጊዜ መኖሩን" የሚናገሩት የሕግ አማካሪው፤ ፍርድ ቤት እስረኞቹ ይለቀቁም አይለቀቁም ብሎ ሳይወስን የፖሊስን አስሮ የማቆየት ጥያቄ ካለመቀበል የሚሰጥበት ውሳኔ አለ።
ሕግ አማካሪው ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪን እንዲለቁ ማዘዝን እና ፖሊስ ያቀረበውን የጊዜ ቀጠሮ አልቀበልም ማለትን "እሁድና ሰንበት" እንደማለት ነው ሲሉ ይገልፁታል። ያው ተመሳሳይ ናቸው ለማለት።
በዚህ ጊዜም ፖሊስ ተጠርጣሪን ለመልቀቅ ይገደዳል።
አቶ ታምራት ይህንን ሲያብራሩ "ሕገ መንግሥቱ ከ48 ሰዓት በላይ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ተጠርጣሪዎችን እንዲያቆይ ስለማይፈቅድለት ፍርድ ቤቱ ልቀቅ የሚል ትዕዛዝ ባይሰጥ እንኳን፤ በእስር እንድታቆይ አልፈቅድልህም ካለው፤ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን አስሮ የሚያቆይበት መብትና ሥልጣን የለውም" ይላሉ።
" ትዕዛዝ የሚያስፈልገው አስሮ ለማቆየት እንጂ ለመልቀቅ ትዕዛዝ አያስፈልግም" የሚሉት አቶ ታምራት፤ ይህ ግን ላለፉት 50 ዓመታት የሚታይ የአሰራር ችግር መሆኑን ይናገራሉ።
ፖሊሶች ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎቹን እንዲያቆይላቸው ይጠይቁና ፍርድ ቤቱ አልፈቅድላቸው ሲል "ልቀቁ አላለንም" በማለት ይዞ የመቆየት ነገር አለ፤ ይህ ግን "ሕገ ወጥ አሰራር ነው" ይላሉ የሕግ አማካሪው።
ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በእስር ለማቆየት ፍርድ ቤት አልፈቅድም በሚልበት ጊዜ ተጠርጣሪዎችን በሌላ ወንጀል ከስሶ እንደገና በ48 ሰዓት ውስጥ መልሶ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይታያል። ይህ ግን አንዳንዴ 'ተንኮል' ሊሆን እንደሚችልም አቶ ታምራት ይናገራሉ።
ነገሩ ሁል ጊዜ ተንኮል ብቻ ላይሆንም እንደሚችሉ የጠቆሙት የህግ ባለሙያው በተጠርጣሪው ላይ ሌሎች አዳዲስ ክሶች ተከታትለው ሊመጡ የሚችሉበት ሁኔታም እንደሚፈጠርም ያስረዳሉ።
እነዚህ ክሶችም ከመጀመሪያው ክስ ጋር የማይገናኙ ራሳቸውን የቻሉ ወንጀሎች ሊሆኑ ስለሚችሉ በዚህ ጊዜ እንደገና በ48 ሰዓት ውስጥ ፖሊስ ፍርድ ቤት አቅርቦ ለማጣራት ተጨማሪ ጊዜ ሊጠይቅ ይችላል።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን በጥርጣሬ መመልከትና በደንብ ማጣራት እንዳለበት ይመክራሉ።
"በተለይ ፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረበው ክስ ከመጀመሪያው ክስ ጋር የሚመሳስል ከሆነ ያው ነው" ሲሉም እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ሲገጥሙ ፍርድ ቤቱ በደንብ ሊመለከተው እንደሚገባ ይናገራሉ።
ይህ ካልሆነ ግን ሰዎች መብታቸውን ተነፍገው ለመጉላላት እንደሚዳረጉም አቶ ታምራት ገልፀዋል።
የሕግ አማካሪው እንዳሉት ምንም እንኳን ፍርድ ቤት አንድን ተጠርጣሪ ይለቀቅ ካለ መልቀቅ ያለበት ፖሊስ ቢሆንም አቃቤ ሕግ የበላይ ተቆጣጣሪ እንደመሆኑ ፖሊስ ሳይፈቀድለት ሰዎችን ይዞ ካስቀመጠ ልቀቅ ብሎ የማዘዝ ሥልጣን አለው። ይህ ግን ብዙ ጊዜ በተግባር ላይ ሲውል እንደማይታይ አቶ ታምራት ትዝብታቸውን አክለዋል።
ይህ ሁሉ ሆኖ መፍትሔ ካልተገኘ ግን ሌላ የሕግ አግባብ መኖሩንም አቶ ታምራት ጠቁመዋል።
ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ እንዲታስሩ አልፈቅድም ብሎ መዝገቡን ከዘጋ፤ ፖሊስም አልለቅም ካለ በአቃቤ ሕግም ሆነ በበላይ ፖሊሶች መፍትሔ ካልተገኘ በፍትሐብሔር መጠየቅ እንደሚቻል አቶ ታምራት ያስረዳሉ።
ከሕግ ውጭ ተይዞ የመገኘት ጉዳይ በሚጣራበት በፍትሐብሔር በመደበኛው ፍርድ ቤት "የእስር ሕጋዊነት ይጣራልኝ" በማለት የተጠርጣሪው ዘመድ፣ ቤተሰብ ወይም ማንኛውም ጉዳዩ ይመለከተኛል ያለ ክስ መመስረት ይችላል። ለዚህም ከተጠርጣሪው ምንም ዓይነት ውክልና አያስፈልግም።
የፍትሐብሔሩ ፍርድ ቤትም ፖሊስ ተጠርጣሪውን በምን አግባብ ይዞ እንዳቆየው አጣርቶ ተጠርጣሪው እንዲለቀቅ የሚያዝበት ሥርዓት መኖሩን የሕግ አማካሪና ጠበቃው አቶ ታምራት ኪዳነማሪያም አስረድተዋል።
Comentários