የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መጠሪያውን እና የብሮድካስት መብቱን ሊሸጥ ነው
- GH ETHIO NEWS
- Aug 22, 2020
- 2 min read
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ማስተላለፍ እንዲችሉ ጨረታ ማውጣቱን ገለፀ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፤ ማህበሩ ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን ለመሸጥ አቅዶ ጨረታ ማውጣቱን ተናግረዋል።
አንደኛው፤ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሮችን በቴሌቪዥን ለማሰራጨት የብሮድካስቲንግ መብቱን ለመሸጥ በማሰብ የዓለም አቀፍ እንዲሁም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃኖች እንዲወዳደሩ ጨረታ ማውጣቱን ገልፀዋል።
ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ኩባንያ የሚጠራበትን ስም ለመሸጥ ጨረታ ማውጣታቸውን አቶ ክፍሌ ሰይፈ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በፕሪሚየር ሊጉ የሚሳተፉ 16 ቡድኖች በጋራ ያቋቋሙትና በንግድ ድርጅትነት የተመዘገበ ማህበር መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ጨምረው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምከንያት በዝግ ስታድየም የሚታይ ከሆነ፣ እንዲሁም ምርመራ እንዲደረግ ግዴታ የሚቀመጥ ከሆነ ተጨማሪ ወጪ ስለሚጠይቅ እነዚህን ነገሮች ለመሸፈን በማሰብ የተለየ አማራጭ ማሰባቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
ከሽያጩ የሚገኘው ገንዘብ የአክሲዮን ማህበሩ አባል ቡድኖች ከመንግሥት ድጎማ ተላቅቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ እንዲሁም በአፍሪካም ሆነ በአውሮፓ ደረጃ ያሉ የስፖርት ቡድኖች እንደሚያደርጉት የስፖርት ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዲገቡ መነሻ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ከጨረታው የሚገኘው አብዛኛው ገቢ የሚሰጠው ለእግርኳስ ቡድኖቹ መሆኑን የተናገሩት አቶ ክፍሌ፣ ቀሪው የድርጅቱ ሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ለመሸፈን ይውላል ብለዋል።
ማሕበሩ የተቋቋመው የእግር ኳስ ቡድኖቹ ከመንግሥት ድጎማ ነፃ እንዲወጡ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ በፕሪሚየር ሊጉ ከሚሳተፉ 16 ክለቦች መካከል ሁለቱ ቡድኖች ብቻ የራሳቸውን ወጪ በመሸፈን የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ደጋፊ አካላት (ስፖንሰርሺፕ) እንዳላቸው ገልፀዋል።
ቀሪዎቹ 14 የእግር ኳስ ቡድኖች የከተማ ክለቦች ወይም ስፖንሰር የሌላቸው መሆናቸውን በመጥቀስ እነዚህን ቡድኖች በገቢ ራስን ማስቻል የዚህ ማህበር ቀዳሚ ዓላማ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ቡድኖች ችግሮች እንዳለባቸው የሚጠቅሱት ኃላፊው፣ በአመራር ችግር ደሞዝ የማይከፈላቸው በመኖራቸው ከጨረታው የሚገኘው ገንዘብ አብዛኛው ለክለቦች እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
ይህንን የገቢ ክፍፍልን በሚመለከት የማስፈፀሚያ ሰነድ ተዘጋጅቶ 16ቱም ክለቦች መስከረም ወር ላይ ውይይት ካደረጉበት በኋላ የሚፀድቅ መሆኑንም ጨምረው አስረድተዋል።
ማህበሩ በርካታ ተጫራቾች እናገኛለን ብሎ ያሰበው ከዓለም አቀፍ ተጫራጮች መሆኑንም ለቢቢሲ ገልፀዋል። በጨረታው ላይ የአገር ውስጥ ድርጅቶችም እንደሚሳተፉ የገለፁት አቶ ክፍሌ በሚወዳደሩበት ወቅት ምክረ ሃሳብ አዘጋጅተው ገቢ የሚያገኙበትን መልክ እና የድርሻ ክፍፍሉ ምን እንደሚመስል ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፟።
በኢትዮጵያ እግርኳስ ረዥም ታሪክ ቢኖረውም፣ የእግር ኳስ ጨዋታዎች ከማይሸጥባቸው የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
Comments