ፑቲን አስመርዘውታል ተብሎ የሚጠረጠረው ተቃዋሚ 'ነፍስ ውጪ-ነፍስ ግቢ' ላይ ነው።
- GH ETHIO NEWS
- Aug 21, 2020
- 3 min read
ፑቲንን በድፍረት በመተቸትና የሚታወቀው የተቃዋሚ መሪ አሌክሴ ናቫልኒ
ማንም አይደፍራቸውም የሚባሉት የሩሲያው ቪላድሚር ፑቲንን በድፍረት በመተቸትና በማብጠልጠል የሚታወቀው የተቃዋሚ መሪ አሌክሴ ናቫልኒ ከትናንት ጀምሮ ‹ነፍስ ውጪ-ነፍስ ግቢ› ላይ ይገኛል።
አሌክሴ አሁን በአንድ የሳይቤሪያ ሆስፒታል ውስጥ ሲሆን ራሱን እንደሳተ ነው ያለው። ጀርመን እና ፈረንሳይ እኛ እናክመው የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ጀርመን የአየር አምቡላንሷን ወደ ሩሲያ ልካ ነበር።

የተሟላ የሕክምና መሣሪያዎች የተገጠሙለትና ምርጥ ሐኪሞችን የያዘው አውሮፕላን ከጀርመን ተነስቶ ሳይቤሪያ ቢደርስም፤ አሌክሴ ከሳይቤሪያ ወጥቶ ጀርመን እንዲታከም የመፈቀዱ ውሳኔ መቀልበሱ ተሰምቷል። የሆስፒታሉ ሐኪሞች አሌክሴ ወደ ጀርመን ሄዱ እንዲታከም እንደማይፈቅዱ እየተነገረ ነው።
አሌክሲን እያከሙ ከሚገኙት ዶክተሮች አንዱ ‹‹አሌክሴ ወደ አምቡላንስ ለመግባት የሚሆን አቅም የለውም›› ብለዋል።
የአሌክሴ ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ግን አሌክሴ ከሳይቤሪያ ሆስፒታል ካልወጣ እንደሞተ ይቆጠራል እያሉ ነው።
‹‹ወደ ጀርመን እንዳይወሰድ የመጣው ውሳኔ ክሬምሊን የአሌክሴን ሕይወት እንዲቋረጥ እንደተወሰነ አድርገን እንቆጥረዋለን›› ብለዋል ደጋፊዎቹ።
አሌክሴን ወደ ጀርመን ለመውሰድና ‹‹ነፍስ ውጭ፣ ነፍስ ግቢ›› ላይ ያሉ ሰዎችን ለማከም በሚረዱ መሳሪያዎች የተሟላችው የአየር አምቡላንስ አውሮፕላን ዛሬ ማለዳ ሳይቤሪያ መድረሷ ተሰምቶ ነበር።
አሌክሴ አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ በሚገኝ አንድ ካፌ ውስጥ ያዘዘው ሻይ ላይ መርዝ ሳይሰጠው አልቀረም ተብሏል።
አውሮፕላን ውስጥ እንደገባ ነው ተዝለፍልፎ የወደቀው። የበርሊኑ ቻራይት ሆስፒታል የፑቲን ቀንደኛ ተቃዋሚ አሌክሴን ለማዳን በሙሉ ዝግጅት እየተጠባበቀ ይገኛል።
የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርከል ‹‹ከኛ ሁሉንም ሕክምና ማግኘት ይችላል፤ ምሕረቱን እንዲያመጣለት እመኛለሁ›› ብለዋል።
የቭላድሚር ፑቲን የክሬምሊን ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ከዚህ ቀደም አሌክሲ ከአገር ውጭ ወጥቶ እንዲታከም እንፈቅዳለን፣ ቶሎ እንዲድንም እነመኛለን ብለው ነበር።
ጀርመን በሩሲያ ለሚመረዙ ተቃዋሚዎች ድጋፍ ስታሳይ ይህ የመጀመርያዋ አይደለም። በ2018 የሩሲያ እውቅ አክቲቪስት ፒዮተር ቨርዚሎቭ በተመሳሳይ ከተመረዘ በኋላ በበርሊን ሕክምና እንዲደረግለት አድርጋለች።
አሌክሴ ናቫልኒን ምንድነው የሆነው?
አሌክሴ ፑቲን የሥልጣን ዘመናቸውን ማራዘማቸውን ሲተች ነበር። ሕገ መንግሥቱን ጥሰዋል፣ ሥልጣን ማራዘማቸው መፈንቅለ መንግሥት ከማድረግ አይተናነስም ሲል ነበር።
ትናንት ከቶምስክ ወደ ሞስኮ እየበረረ ሳለ ከፍተኛ ሕመም ስለተሰማው አውሮፕላኑ በድንገት ኦምስክ፣ ሳይቤሪያ እንዲያርፍ ተገዷል። በ2011 ያቋቋመው ድርጅቱ የጸረ ሙስና ፋውንዴሽን ቃል አቀባይ ኪራ ያርሚሽ ‹‹አሌክሴን መርዝ አጠጡት›› ሲሉ በትዊተር ገለጹ።
ይህን ተከትሎ አሌክሴ በቃሬዛ ከአውሮፕላን ወጥቶ ወደ አምቡላንስ ውስጥ ሲገባ የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቀቀ። ሌላ ቪዲዮ ደግሞ አሌክሴ አውሮፕላን ውስጥ ሳለ በከፍተኛ ስቃይ ሲጮኽ የሚያሳይ የሚረብሽ ምስል ተለቀቀ።
ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ አሌክሴ በቶምስክ አውሮፕላን ጣቢያ ቁጭ ብሎ ሻይ ሲጠጣ የሚያሳይ ፎቶ ተለቀቀ።
የፎቶው ባለመብት,EPA

የምስሉ መግለጫ,የተቃዋሚ መሪው ከአውሮፕላን ወጥቶ ወደ አምቡላንስ ውስጥ ሲገባ የሚያሳይውን ምስል በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ተቀባብለውታል።
አሁን የሚገኝበት ሆስፒታል በሩሲያ የጸጥታ ኃይል የተከበበ ሲሆን ፖሊስ ከሆስፒታል የሱ የሆኑ ንብረቶችን ይዞ ሄዷል።
አሁን አሌክሴ በቬንትሌተር ነው የሚተነፍሰው፣ ራሱን ሙሉ በሙሉ ስቷል፣ ጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛል።
ባለቤቱ ዩሊያ ናቫለናያ መጀመሪያ ወደ ሆስፒታሉ እንዳትገባ ተከልክላ ነበር። ምክንያቱን ስትጠይቅም ታማሚው አልፈቀደም የሚል መልስ ተሰጥቷት ነበር። በኋላ ግን ገብታ እንድታየው ተፈቅዶላታል።
እያከሙት ያሉት ሐኪሞችም እሱ ያለበትን ሁኔታና ምን እንደገጠመው ለሚዲያ ለመናገር ፍርሃት ይዟቸዋል። በክሬምሊን ይደገፋሉ የሚባሉ ሚዲያዎች አሌክሴ ባለፈው ሌሊት መጠን ሲጠጣ ነበር የሚል ዜና የለቀቁ ሲሆን ባለቤቱ ግን ይህ የተቀነባበረ ነጭ ውሸት ነው፤ ወንዝ ወርዶ ሲዋኝ ነበር ያመሸው ብላለች።
አሌክሲ ናቫልኒ ማን ነው?
አሌክሴ በሩሲያ ውስጥ እውቅና ያገኘው የባለሥልጣናትን ሙስና በማጋለጥ ነው። በዚህም በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጓል። የፑቲንን ፓርቲ የሞሉት ሸፍጠኞችና ሌቦች ናቸው ይላል አሌክሲ።
በ2011 የፑቲን ዩናይትድ ራሺያ ፓርቲ ምርጫ አጨበርብሯል ብሎ በማጋለጡ ለ15 ቀናት ታስሮ ነበር። በ2013 አሌክሴ በሙስና ክስ ተመስርቶበት ለአጭር ጊዜ ከታሰረ በኋላ ተለቋል።
በ2018 ፑቲንን ለመገዳደር ምርጫ ቅስቀሳ ቢጀምርም ቀደም ሲል በነበረበት የምዝበራ ክስ ምክንያት መወዳደር አትችልም በሚል ታግዷል።
በ2019 ፑቲንን የሚቃወም ትልቅ ሰልፍ በመጥራቱ ሕገ-ወጥ የሰልፍ ጥሪ አድርገሀል በሚል ለ30 ቀናት ታስሯል። ያን ጊዜ በእስር ላይ ሳለ ባልተለመደ ሁኔታ ሕመም ገጥሞት ነበር።
ሐኪሞች የቆዳ አለርጂ የሚመስል ነገር ቢጠቅሱም እሱ ግን አለርጂ ኖሮበት እንደማያውቅ ተናግሮ ነበር። በኋላ ላይ ግን የገዛ ሐኪሞቹ ለአንዳች መርዝነት ላለው ነገር ተጋልጠህ ነበር ሲሉ ነግረውታል።
ምናልባት እስር ቤት ሳለ እሱን መርዞ ለመግደል ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ይገመታል።
ቪላድሚር ፑቲን ከዚህ ቀደም በርከት ያሉ ተቃዋሚዎቻቸውን፣ የስለላ መኮንኖችን፣ ጋዜጠኞችን በጠራራ ጸሐይ በማስገደል እና በሰው አገር ጭምር ሄደው በመመረዝ ስማቸው ይነሳል።
コメント